አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥትን የልማት ስትራቴጂ በመከተል የግል ሴክተሩም በከፍተኛ ፍጥነትና ተነሳሽነት አብሮን እየሰራ ይገኛል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ውብና ማራኪ ተደርጎ በ1 ነጥብ 3 ሄክታር ቦታ ላይ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለህዝብ የተገነባው የሳር ቤት ፕላዛ ትናንት ተመርቆ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በከተማችን የምናከናውናቸው የልማት ስራዎች ለሰው ልጅ ክብርና ጥቅም የሚሰጡ፣ የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ እንዲሁም የከተማችን ነዋሪዎች ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩባቸው ናቸው ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከራሱ የግል ይዞታ 1 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት በመወሰን አልምቶ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውል ማድረጉ ጠቅሰው፤ ይህም አዲስ እሳቤና ትልቅ ለውጥ መሆኑን አመልክተዋል።
ሚድሮክ የወንዝ ዳር ልማትም ስንሰራ አብሮን የሰራ ስለሆነ በከተማችን ነዋሪዎች እና በራሴ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ያሉት ከንቲባዋ፤ የመንግሥትን የልማት ስትራቴጂ በመከተል የግል ሴክተሩም በከፍተኛ ፍጥነትና ተነሳሽነት አብሮን እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

