Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአትሌቶች የተሰጠው እውቅና ተተኪዎችን የሚያበረታታ ነው – ቀነኒሳ በቀለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ለአንጋፋ አትሌቶች የሰጠው እውቅና ተተኪ አትሌቶችን የሚያበረታታ ነው አለ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት መርቀው በከፈቱት የአዲስ ስፖርት ፓርክ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ 15 የኦሊምፒክ ጀግኖች የክብር ሐውልት እንደቆመላቸው ይታወቃል፡፡

አትሌቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መልዕክት፥ ለአንጋፋ አትሌቶች የተሰጠው እውቅና ተተኪዎችን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግሯል፡፡

እንደዚህ አይነት የስፖርት ማዕከላትን በኢትዮጵያ ማየት የዘወትር ህልሙ እንደነበር የገለፀው አትሌቱ፥ ምኞቴ እውን ሆኖ በመመልከቴ ደስተኛ ነኝ ብሏል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የክብር ሐውልት ተሰርቶላቸው እውቅና ከተሰጣቸው አትሌቶች አንዱ በመሆኑ ኩራት እንደተሰማው ገልጿል፡፡

ፓርኩ የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ እና የቴኒስ ሜዳዎች እንዲሁም የመሮጫ መም ያካተተ መሆኑን አንስቷል፡፡

የስፖርት ፓርኩ እውን እንዲሆን እና ለአትሌቶቹ ክብር እንዲሰጥ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርቧል፡፡

Exit mobile version