Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጎተራ ክላውድ – የኢትዮጵያ የዲጂታል ሉዓላዊነት እና የመረጃ በላይነት ማረጋገጫ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመናችን ትልቁ ሀብት እና ኃይል “መረጃ” (Data) ነው። ይህንን መረጃ መቆጣጠር ደግሞ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ያህል ትልቅ ትርጉም አለው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በራሱ አቅም የገነባው የ“ጎተራ ክላውድ – G-Cloud” መሠረተ ልማት፣ የሀገራችንን መረጃ ደሕንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ለማከማቸት እና ለማስተዳደር የተቋቋመ የቴክኖሎጂ ምሽግ ነው።

የኢትዮጵያ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ስኬታማ እንዲሆን አስተማማኝ የዲጂታል መሰረተ ልማት የግድ ይላል።

ጎተራ ክላውድ የኢ-መንግስት (e-Government)፣ የዲጂታል ፋይናንስ እንዲሁም የተለያዩ ዘርፎች አገልግሎቶቻቸውን በዘመናዊ እና ፈጣን ቴክኖሎጂ ለዜጎች እንዲያቀርቡ በማድረግ የስትራቴጂውን ግብ ለማሳካት ቁልፍ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ስንመለከት እንደ አውሮፓ ሕብረት (በ GDPR – The General Data Protection Regulation ህግ)፣ ቻይና እና ሌሎችም በቴክኖሎጂ ያደጉ ሀገራት የዜጎቻቸውን እና የተቋማቶቻቸውን ሚስጥራዊ መረጃዎች በውጭ ሀገር ሰርቨሮች ላይ ማከማቸትን ይከለክላሉ።

መረጃን በሀገር ውስጥ ማከማቸት (Data Localization) የብሔራዊ ደሕንነት ጉዳይ አድርገው ይወስዱታል።

ኢመደአ የገነባው ጎተራ ክላውድም ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ የደሕንነት ስታንዳርድ እንድትተገብር እና መረጃዎቿን በራሷ ቁጥጥር ስር እንድታደርግ አቅም ፈጥሮላታል።

ጎተራ ክላውድ (G-Cloud) ምን ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል?

የክላውድ አገልግሎት ኮምፒውተር፣ ስቶሬጅ፣ ኔትወርክ እና ሶፍትዌሮችን በኢንተርኔት ለማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሲሆን÷ ጎተራ ክላውድ በከፍተኛ የደሕንነት መርሆች የሚከተሉትን አገልግሎቶች ይሰጣል፡-

• IaaS (Infrastructure as a Service): የመሰረተ ልማት አገልግሎት
• PaaS (Platform as a Service): የፕላትፎርም አገልግሎት
• SaaS (Software as a Service): የሶፍትዌር አገልግሎት
• Backup & Recovery: የመረጃ ክምችት እና መልሶ ማግኛ አገልግሎት

ይህንን የሀገር ውስጥ የክላውድ አገልግሎት መጠቀም፡-
1. ተቋማት የራሳቸውን ውድ የሆነ ዳታ ማዕከል (Data Center) ለመገንባት የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ እና የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል።

2. ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በመቀነስ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ነፃነትን ያረጋግጣል።

3. የመረጃ ደሕንነትን ከማንኛውም የውጭ ጥቃት እና የመረጃ ስርቆት በከፍተኛ ደረጃ ይጠብቃል።

በአጠቃላይ ጎተራ ክላውድ ፈጣን፣ የተቀናጀ እና ውጤታማ የዲጂታል አገልግሎት አቅርቦትን በማስቻል የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የመረጃ በላይነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ሀገራዊ ሀብት ነው።

መረጃውን ያገኘነው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት አስተዳደር ነው።

Exit mobile version