አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጀመሩ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ የሕዝቡ ድጋፍ ወሳኝ ነው አሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፡፡
ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመትና የመጋቢት 24 ትሩፋቶችን የሚዘክር ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በቦንጋ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ስልፍ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሀገራዊ ለውጡ በዘርፈ ብዙ ድሎች የታጀበ መሆኑን ተናግረዋል።
መጋቢት 24 አካታችና ሕብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ መሠረት የተጣለበት፣ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው የህግ ማሻሻያዎች የተደረገበት እንደሆነ አመላክተዋል።
በለውጡ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መተግበራቸውንና የዘመናት የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸው÷ የክልሉ መመሥረትም የለውጡ አንዱ ትሩፋት ነው ብለዋል።
የለውጡ መንግሥት በሁሉም ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች ማስመዝገቡን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የተጀመሩ የልማትና የሰላም ግንባታ ተግባራት ከግብ እንዲደርስ ሕዝቡ በጽናት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግሥት ምላሽ ያላገኙ የሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

