Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የግብርና ኢንተርፕራይዝ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ኢንተርፕራይዝ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ 214 ስራ አጥ ወጣቶች በ2017 ዓ.ም ተደራጅተው የጀመሩት የመስኖ ስራ ኢንተርፕራይዝ ዛሬ ላይ ከራሳቸው አልፈው ለበርካቶች የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢንተርፕራይዙ ሊቀመንበር ወጣት አባይ ታደሰ በህንፃ ኤሌክትሪክ ዝርጋታ በዲፕሎማ ተመርቆ ለ6 ዓመታት ስራ አጥ እንደነበር በማስታወስ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ቅጥርን ከመጠበቅ ይልቅ ተደራጅተው በግብርና ልማት ስራ ላይ ቢሰማሩ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ መክሯል፡፡

ስራውን ከመጀመሩ በፊት ቤተሰቡን በአግባቡ ማስተዳደር ይቸግረው እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ኑሮው እየተሻሻለ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በቀጣይ የኢንተርፕራይዙን ስራ አጠናክሮ በመቀጠል ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝም አመልክቷል።

ፎሶሊያ፣ አተር እና ብሮክሊን እያለሙ የሚገኙት ወጣቶቹ ባለፈው ዓመት ብቻ በ43 ሄክታር መሬት ላይ ከ1 ሺህ ኩንታል በላይ ፎሶሊያ፣ 2 ሺህ 395 ኩንታል አተር እና 877 ኩንታል ብሮክሊን በማልማት 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ማትረፍ ችለዋል፡፡

ወጣቶቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት ባሻገር ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ሲሆን÷ ከኢንተርፕራይዙ አባላት ባለፈ ለ500 ሰዎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

መንግሥት ለኢንተርፕራይዙ 78 ሄክታር መሬት በመስጠት፣ የመስኖ ውሃ በማውጣት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ድጋፍ ማድረጉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

Exit mobile version