Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናዊ ደኅንነት እና ለጋራ ብልፅግና…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ደኅንነት፣ ለቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው አሉ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ”የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጣና የባሕር አስተዳደር፤ አካታችነትና ትስስር ለጋራ ጥቅም” በሚል መሪ ሐሳብ 4ኛውን ዓመታዊ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ሉዓላዊ መዳረሻ ጥያቄ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ስትራቴጂክ መሰረትና ቅቡልነት ያለው ነው።

ኢትዮጵያ ከባሕር በር መዳረሻዎቿ የተገለለችበት ኢፍትሕዊ በደል በቀጣናው የሚጠበቅባትን ገንቢ ሚና እንዳትጫወት መገደቡን ገልጸው÷ የሀገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝብን የልማት ፍላጎት ለማሳለጥ አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ የባሕር ኃይል በመገንባቷ የባሕር ላይ ውንብድናን፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን፣ ሽብርተኝነትና መሰል ስጋቶችን ለመዋጋት ከፍተኛ የትብብር አቅም ይሆናልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕርና ኤደን ባሕረ ሰላጤ ሉዓላዊ መዳረሻ ፍላጎትና ጥያቄም ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ደኅንነትን በማረጋገጥ ለቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና የላቀ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው÷ የቀይ ባሕርና ኤደን ባሕረ ሰላጤን ዘላቂ ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ሁሉንም ሀገራት የሚያሳትፍ የባሕር ላይ አስተዳደር መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ቀጣናዊ ትስስርን በማጎልበት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተመሰረተ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም የንግድ መዳረሻ ወደቦችን ኢኮኖሚያዊ አስተሳሳሪነታቸውን የሚያጠናክር ወሳኝ የውሃ ላይ የአስተዳደር ሥርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

በውይይቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎን (ዶ/ር) ጨምሮ ተጋባዥ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version