Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ግሪክ ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ማሕበራዊ ሚዲያን ልትከለክል ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግሪክ መንግሥት ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ማሕበራዊ ሚዲያን አጠቃቀምን የሚከለክል አዲስ ሕግ አውጥቷል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ ማሕበራዊ ሚዲያ የአዕምሮ ጭንቀት፣ የእንቅልፍ ማጣት እና ሌሎች ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰው÷ ውሳኔውም ታዳጊ ሕጻናትን ለመጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ አዕምሮ እረፍት እንዳያገኝ እንደሚያደርግ ገልጸው÷ በዚህም ልጆች በስልኮቻቸው ላይ ብዙ ጊዜ በማሳለፍ ጥሩ እንቅልፍ እንደማያገኙና የበለጠ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገቡ አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማሕበራዊ ሚዲያ መጠቀምን የሚከለክለው አዲስ ሕግ ከፈረንጆቹ ጥር 1 ቀን 2027 ጀምሮ እንደሚተገበር ተመላክቷል።

ሀገሪቱ ከዚህ በፊት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሞባይል ስልኮችን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል እገዳ ተግባራዊ አድርጋ እንደነበርና ወላጆችም የልጆች ስክሪን አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መንገዶችን በመፍጠር ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን z ኢንዲፔንደንት ዘገባ አመላክቷል።

አውስትራሊያ ባለፈው ዓመት ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ማሕበራዊ ሚዲያን የከለከለች የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን÷ እንደ ስሎቬኒያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኦስትሪያ እና ስፔን ያሉ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ተመሳሳይ እገዳ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version