Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በለውጡ መንግሥት የተገነቡ ከ53 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ53 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች መገንባት ተችሏል አለ።

ተቋሙ ክልሎችን እርስ በርስ የሚያገናኝና ሀገራዊ የንግድ ኮሪደሮችን የሚያጠናክር የፌዴራል የመንገድ መረብ የመዘርጋት ተልዕኮውን በማሳካት ረገድ ባለፉት ስምንት ዓመታት አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

በዚህም በ2010 ዓ.ም የነበረው የ126 ሺህ 773 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን በ2018 ዓ.ም አጋማሽ ወደ 180 ሺህ 232 ኪሎ ሜትር ማደግ ችሏል።

ይህም ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ ከ53 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዲስ መንገድ የጨመረ መሆኑ ተመልክቷል።

የመንገድ ጥግግቱ በየ1 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ከ115 ነጥብ 2 ወደ 157 ኪሎ ሜትር አድጓል።

በዘርፉ በለውጡ ዓመታት ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከልም ኢትዮጵያን የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያደርጉ ግዙፍ የፍጥነት መንገዶች እውን መሆናቸው ተጠቃሽ ነው።

ከለውጡ በፊት 84 ነጥብ 7 ኪ.ሜ የሚረዝመው የአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድ አሁን ላይ የሞጆ-መቂ-ባቱ- ነገሌ አርሲ (151 ኪሎ ሜትር) እና የድሬዳዋ-ደዋሌ (220 ኪሎ ሜትር) የፍጥነት መንገዶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ፣ ጅማ፣ ደብረ ማርቆስ እና ነቀምቴ የሚዘልቁ አራት አዳዲስ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጸው የመንገዶች አስተዳደር÷ ይህም ኢትዮጵያን በ10 ዓመታት ውስጥ የ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ባለቤት ለማድረግ ለተያዘው ግብ ትልቅ ርምጃ ነው ብሏል።

እንዲሁም ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ 182 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ በማድረግ የ71 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነዋል።

ተቋሙ የመንገድ ጥራትን ከመጠበቅ አንጻርም 80 ሺህ 37 ኪሎ ሜትር መደበኛ ጥገና እና 3 ሺህ 35 ኪሎ ሜትር ከባድ ጥገና በማከናወን የሀገሪቱን የመንገድ ሀብት የመንከባከብ ስራ በትኩረት ሰርቷል።

ተቋማዊ አደረጃጀትን በማዘመን ረገድም ቀደም ሲል ተነጥለው የነበሩ የመንገድ ጥገና ዲስትሪክቶችና ሴክሽኖች ወደ አስተዳደሩ እንዲመለሱ በማድረግ የፕሮጀክቶችን ክትትልና ድጋፍ ለማጠናከር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ተከፍተዋል።

በተጨማሪም የከባድ ተሽከርካሪዎችን ጫና ለመቆጣጠር የሚረዱ የሚዛን ጣቢያዎች ዲጂታላይዝ በማድረግ የተሽከርካሪዎችን ክብደት ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ በመመዝገብ፣ የአሰራር ግልጽነትን በማስፈንና የመንገድ ብልሽትን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ስራዎች ተሰርተዋል።

ተቋሙ የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማጎልበትም በቢሊየን የሚቆጠር ብር ወጪ የተደረገባቸው ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ ማሽነሪዎች ግዢ መፈጸሙን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል።

Exit mobile version