Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ትርጉም አልባ ያደርገዋል አለች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት ከአሜሪካ ጋር የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ትርጉም አልባ እንደሚያደርገው አስጠንቅቃለች፡፡

የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በሊባኖስ ላይ እየደረሰ ያለው የእስራኤል ጥቃት ከአሜሪካ ጋር የተደረገውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ትርጉም የለሽ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ላይ የሚፈጽመው ጥቃት የቀጠለ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ብቻ 254 ሰዎች ሲገደሉ 1 ሺህ 165 ሰዎች መቁሰላቸው ነው የተዘገበው፡፡

ሊባኖስ እና ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን፤ ማንኛውንም ስምምነት መጣስ ጠንካራ ምላሽ እንደሚያሰጥ አስጠንቅቀዋል፡፡

ኢስላማባድ እና ቴህራን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊባኖስን እንደሚያጠቃልል ቢናገሩም ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ ግን ያንን ማስተባበላቸው ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ እና የኢራን ልዑካን ቋሚ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ በኢስላማባድ ድርድር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት በማውገዝ የንጹሃን ዜጎች ጥቃት እንዲቆም የጠየቀችው ቱርክዬ ቀጣናውን ለማረጋጋት እና የሊባኖስን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደምትደግፍ ገልጻለች፡፡

ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱ መጣሱን ስትገልፅ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያን ኔታንያሁ በበኩላቸው እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ ጥቃት መፈጸሟን እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነትን ሙሉ በሙሉ እስክታከብር ድረስ የአሜሪካ ኃይሎች በአካባቢው እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version