አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ለትንሳኤ በዓል በቂ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ለገበያ እየቀረበ ነው አለ።
የቢሮው ኃላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ በትኩረት በመሠራቱ የእርድ ከብት፣ የወተት፣ የዶሮ እና የእንቁላል ምርት በቂ አቅርቦት ተፈጥሯል።
በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ማዕከላት የገበያ እጥረት እንዳይከሰት ቅድመ ዝግጅት መደረጉንና ጥራት ያለው ምርት ለገበያ ለማቅረብ የተሠራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርት አቅርቦቱን ከትራንስፖርት ችግር ጋር በማያያዝ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚሞክሩ አቅራቢዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዓመቱን ሙሉ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሠራባቸው ዘርፎች መካከል የወተት ልማት መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በቂ ምርት እየቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከክልሉ ፍጆታ ባለፈም በቀን ከ240 ሺህ ሊትር በላይ ወተት ለማዕከላዊ ገበያ እየተላከ እንደሚገኝ ኃላፊው አንስተዋል።
በደሳለኝ ቢራራ

