አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ዋጋቸው 28 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና የንግድ ማጭበርበሮች ባለፉት ስድስት ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊየን ብር የሚገመተው የኮንትሮባንድ እቃ በህገ-ወጥ መንገድ ከሶማሌላንድ ወደ ጅግጅጋ በጭነት መኪና ሲጓጓዝ የተያዘ ሲሆን፤ ሊሰወር የነበረ 15 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ቀረጥና ታክስ በኮምቦልቻ፣ በሞጆ እና በቃሊቲ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ክትትል ተደርሶባቸው ለመንግስት ገቢ ተደርጓል፡፡
ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የውጭ ምርት የሆነ ማሽላ የእርዳታ እህል በማስመሰል የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ሳይፈጸምበት ሲጓጓዝ ተይዟል፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ የተለያዩ አልባሳት እና የግንባታ ዕቃዎች እንደሚገኙበት ያስታወቀው ሚኒስቴሩ ፤ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚገመት በጎብኚ ስም የገባ የኮንትሮባንድ እቃ በድሬዳዋ የጉምሩክ ቅርንጫፍ መያዙን ገልጿል፡፡
ሌሎች ግምታዊ ዋጋ ያልወጣላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችም በተጠቀሰው ጊዜ መያዛቸው ነው የተነገረው፡፡
ህጋዊ ንግድን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀሙ የንግድ ማጭበርበሮች ለመከላከል በኮምቦልቻ፣ በሞጆ እና ቃሊቲ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች በመሆናቸው በሌሎችም ቅርንጫፎች መጠናከር እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

