አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓልን በጸሎት፣ በምስጋና እና በሌሎች ሥርዓቶች እያከበሩት ይገኛሉ።
በዚሁ ወቅት የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች፥ ስቅለት ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም የገባው ቃል ኪዳን የተፈጸመበት እንዲሁም የፍቅር እና የድኅነት ዕለት ነው ብለዋል።
በዚህም ምዕመናን ለሌሎች መኖር፣ ትህትናንና ፍቅርን በመማር የጽድቅን መንገድ መምረጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ስቅለት ኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ምህረት የማለደበት ነው ያሉት አባቶቹ፤ እኛም ይቅርታን የህይወታችን አካል ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው መከራ እና ስቃይ ለሰው ልጆች ደህንነትና ነጻነት መገኘት መሰረት በመሆኑ እኛም በመተሳሰብ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ተምሳሌት መተግበር ያስፈልገናል ብለዋል።
በበዓሉ ስለ ስቅለቱ የሚያወሱ ምንባባት እየተነበቡ ሲሆን በስብከት እና በዝማሬም ዕለቱ እየታሰበ ይገኛል።
በመሳፍንት እያዩ

