Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ625 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልበ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ625 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡

የክልሉ መንግስት ይቅርታ ካደረገላቸው 625 የሕግ ታራሚዎች መካከል 32ቱ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ  እንዳስታወቁት÷ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ ምግባር የነበራቸው እና በሕግ የተደነገገውን የይቅርታ መስፈርት ያሟሉ ናቸው፡፡

የይቅርታው ተጠቃሚዎች ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የቆዩ፣ ከተፈረደባቸው ፍርድ ቢያንስ አንድ ሶስተኛ የፍርድ ጊዜ ያጠናቀቁ እንዲሁም በማረሚያ ተቋማት ስለመታረማቸውና ስለመልካም ባህሪያቸው ማረጋገጫ የቀረበላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የይቅርታው ተጠቃሚዎች ከተጎጂ ወገኖች ጋር ታርቀው የእርቅ ሰነድ ማቅረባቸው የተረጋገጠ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ርዕሰ መተዳድሩ የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የሕግ ታራሚዎች የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን የበደሉትን ህብረተሰብ የሚክሱ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህብረተሰቡም በይቅርታ የተለቀቁት የሕግ ታራሚዎች በፈፀሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ መታረማቸውን በመረዳት መልካም እና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version