Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አርሰናል ከቦርንማውዝ…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን 8 ሰዓት 30 ላይ አርሰናል በኢምሬትስ ቦርንማውዝን ያስተናግዳል፡፡

የሊጉ መሪ አርሰናል በሊጉ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት እና መሪነቱን ለማጠናከር ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡

ያለፉትን አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ተጋጣሚው ቦርንማውዝ በበኩሉ÷ ወደ ድል ለመመለስ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቱም በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ድል ሲያደርጉ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡

አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ማንቼስተር ሲቲ እስኪጫወት ድረስ የነጥብ ልዩነቱን ወደ 12 ከፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

የሊጉ ጨዋታ ሲቀጥል ምሽት 1 ሰዓት 30 ላይ ሊቨርፑል አንፊልድ ሮድ ፉልሃምን ይገጥማል፡፡

ሊቨርፑል በሊጉ ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል፡፡

ተጋጣሚው ፉልሃም በበኩሉ÷ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት የሚያደርገው ፉክክር ተጠባቂ ነው፡፡

አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ በርንሌይ ከብራይተን እንዲሁም ብሬንትፎርድ ከ ኤቨርተን ሌሎች በሊጉ የሚደረጉ የዛሬ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

ትናንት ምሽት በተደረገ የሊጉ ጨዋታ ዌስትሃም ዩናይትድ ወልቭስን 4 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል፡፡

ሊጉን አርሰናል በ70 ነጥብ ሲመራው ማንቼስተር ሲቲ 61፣ ማንቼስተር ዩናይትድ 55 እንዲሁም አስቶንቪላ በ54 ነጥብ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version