አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ተቋሙ ባስተላለፈው መልዕክት÷ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብሏል፡፡
ትንሳኤ የእግዚአብሔር ታላቅ ርህራሄ እና ፍቅር የተገለጠበት፣ ሞት የተሸነፈበት፣ ለዘመናት በሞት ጥላ ስር ሲኖር ለነበረው የሰው ዘር ታላቅ የሕይወት ብርሃን የበራበትና በሰይጣን እስራት ውስጥ ለነበሩ መፈታት የተበሰረበት ታላቅ የመፈታት እና የነፃ መውጣት የድል በዓል መሆኑን ገልጿል።
ክርስቲያኖች በዓሉን ሲያከብሩ ኢየሱስ ከርስቶስ ለሰው ልጅ የከፈለውን የፍቅር ዋጋ በማሰብ፣ እርሱ ያስተማረውን እና ያሳየንን የጽድቅ ሕይወት በጽናት በመኖር፣ እርስ በእርስ በመዋደድ፣ ጥላቻን በማስወገድ፣ መለያየትን በመጸየፍ፣ ፍቅርን፣ ርህራሄን፣ መከባበርን እና መረዳዳትን እንደ ሸማ በመላበስ ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል።
አሁን ያለንበት ዘመን መለያየት፣ ግጭት፣ ጦርነት እና አደጋ በስፋት እየተከሰተ ያለበት ወቅት መሆኑን በመጥቀስ÷ እነዚህ እና መሰል የክፋት ተግባራት የእምነት ጽናትን በጽኑ እየተፈታተኑ የሚገኝበት ጊዜ እንደሆነም አመልክቷል።
የጌታን ፈለግ በመከተል ለሌሎች መዳን፣ ማደግ እና መኖር ምክንያት መሆን እንደሚገባም አስገንዝቧል።
በዓሉን ስናከብር በክርስትና አስተምህሮና በኢትዮጵያዊ ባህል መሰረት የታመሙትን በመጠይቅ፣ በሕግ ጥላ ስር የሚገኙትን ታራሚዎች በመጎብኘት፣ በተለያዩ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ወገኖቻችን በዓሉን እንደ እኛው በደስታ ማክበር ይችሉ ዘንድ ያለንን በማካፈል ሊሆን ይገባልም ነው ያለው ተቋሙ ባስተላለፈው መልዕክት፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ሰላም በመጸለይ፤ ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት ቃል ኪዳን በመግባት በዓሉን ልናሳልፍ ይገባል ሲልም ተቋሙ ለፋና ዲጂታል በላከው መልዕክት ጥሪ አቅርቧል፡፡

