አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም) ጋር ያላትን ትብብር በምታጠናክርበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከአፍሪኤግዚም ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኢሎምቤ (ዶ/ር) ጋር አፍሪካ ራሷን በምትችልበት ሁኔታ እና ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም አፍሪካ በኢኮኖሚ ራሷን ለመቻል የያዘቻቸው የአጭር እና የረጅም ጊዜ ፕሮግራሞች፣ ለወቅታዊው የዓለም ቀውስ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ቀጣናዊ ትብብር የሚጠናከርበት፣ አህጉራዊ የንግድ ግንኙነት የሚሰፋበት እንዲሁም የአፍሪካን የፋይናንስ አቅም ለማንቀሳቀስ ስለሚቻልበት ሁኔታ ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
የዓለምን ኢኮኖሚ እየፈተነ ስላለው የምርት አቅርቦት መዛባት እንዲሁም የሸቀጥ አቅርቦትን ለማረጋጋት እየተወሰዱ ስላሉ የተቀናጀ አህጉራዊ ኢኒሼቲቮች እና ማክሮኢኮኖሚ ላይ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል።
በውይይታቸው በኢንዱስትሪ፣ የፋይናንስ መሰረተ ልማት እና የፋይናንስ ዘርፍ ላይ መተባበር እንደሚገባ ገልጸው፤ አፍሪኤግዚም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በቅርበት የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች ቅድሚያ በሚሰጣቸው ኢኒሼቲቮች እና ‘ራስን መቻል’ በሚለው የአፍሪካ ራዕይ ላይ ተቀራርበው ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።

