አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ይበልጥ ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባ አዳነች እንዳሉት÷ በመዲናዋ ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ጤናማ እና በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት በቁርጠኝነት መስራት ይገባል፡፡
በከተማዋ የወጣቶችን ስብዕና ከመገንባት ባለፈ በርካታ የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በቅንጅት መሰራቱንም አስረድተዋል፡፡
በሥራ እድል ፈጠራ ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት ከ6 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ከ2 ሚሊየን በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በለውጡ መንግሥት በአዲስ አበባ የተከናወኑ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ዘመኑን የዋጀ ክሕሎትና የዳበረ ስብዕና ያለው ወጣት ማፍራት እያስቻሉ ነው ብለዋል፡፡
በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ ቤተ መጻሕፍትና ሌሎች ማዕከላት ብቁ፣ ጤናማና በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ጠቅሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ በ2012 ዓ.ም አካባቢ 495 የሚጠጉ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ብቻ እንደነበሩ አስታውሰው÷ አሁን ላይ ግን 1 ሺህ 589 መድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡
የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በአስተሳሰብ፣ በአካልና በስብዕና የዳበሩ እንዲሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

