Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 93 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት 9 ወራት በተለያዩ ዘርፎች 93 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል አለ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ።

የቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በግብርና ዘርፍ 44፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ 35 እና በአገልግሎት ዘርፍ 14 የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ተሰጥቷል።

አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሃብቶች አጠቃላይ 3 ቢሊየን 350 ሚሊየን 897 ሺህ 476 ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን ገልጸው÷ ይህም የዕቅዱ 79 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በክልሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች 195 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አንስተው÷ ከ8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በክልሉ ውሳኔ ላገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 7 ሺህ 452 ነጥብ 28 ሄክታር መሬት ማስተላለፍ ተችሏል ያሉት ኃላፊው÷ ነባር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ይዞታን ኦዲት በማድረግ 4 ሺህ 858 ሄክታር ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ጠቁመዋል።

በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለ3 ሺህ 205 ዜጎች ቋሚ እንዲሁም 80 ሺህ 215 ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠራቸውንም ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በገቡት ውል መሠረት የስራ እድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል ድጋፍና ክትትል የማድረግ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆነና ባለሃብቶችም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version