Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅ በኩል የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ውጤት ማሳየት ጀምሯል – የኢትዮጵያ አምባሳደሮች

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅ በኩል የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው ጥሩ ጅምር እየታየበት መሆኑን በሳዑዲ ዓረቢያ እና በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ተናገሩ ።

ችግር ውስጥ የወደቁ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሀገር የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተግባራዊ መደረጉ ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉ ይነገራል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ ከለውጡ በኋላ ለዜጎች ቅድሚያ በሰጠው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር በመነጋገር ችግር ውስጥ የነበሩ እስከ 200 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ከስራ ገበታቸው የተቀነሱ፤ የወር ደመወዛቸውን ተከልክለው ለነበሩ ዜጎች ለመድረስ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል ።
ኤምባሲው ለመጀመሪያ ጊዜ ጠበቃ በማቆም በፍትህ ስርአቱ ለተገፉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ዴዴፎ በበኩላቸው ምንም ሰነድ የሌላቸው 30 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ስራ ለማመቻቸት በኤምባሲው በኩል እንቅስቃሴ ቢጀመርምር የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ እንቅፋት ፈጥሯል ነው ያሉት ።
ሆኖም ለእነዚህ ዜጎች አስፈላጊውን ሰብአዊ እርዳታ የማድረሱ ስራ ግን እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በህጋዊ መልኩ ስራ ገበታቸው ላይ የሚገኙ ዜጎችም ቢሆኑ የስራ ቦታ ዋስትና ማጣት ፈተና ሆኖባቸዋል የሚሉት አምባሳደሩ ፤ መንግስት ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ዜጎች ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ዜጎች ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት እየፈተነ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስን በመቋቋም የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲውን ውጤታማ ለማድረግ ጥረቶች መቀጠላቸውን አውስተዋል ።

አምባሳደሮቹ ለዜጎች አገልግሎት ለመስጠት በራቸውን ክፍት ማድረግ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ጥረቶች መቀጠላቸውን ለፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል ።

በሀይለየሱስ መኮንን

Exit mobile version