አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተሻለ መልክ ያሳደጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
የክልሉ የፓርቲና የመንግሥት የሦስተኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተሻለ መልኩ ያሳደጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በተለያዩ ዘርፎች በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ገልጸው÷ ስራዎቹ በቁጥር ብቻ የሚገለጹ ሳይሆኑ የማሕበረሰቡን ችግር የቀረፉ ናቸው ብለዋል፡፡
የክልሉን የልማት ሥራዎች ለማቀላጠፍ የሚያግዙ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶች መተግበራቸውን ጠቅሰው÷ ሁሉንም የልማት ኃይሎች በማቀናጀት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ውጤታማ ማድረግ ከአመራሩ የሚጠበቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በግምገማው ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና በሥራ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዝርዝር አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም ጠቁመዋል።
ጥንካሬዎች በማስቀጠል እና የነበሩ ክፍተቶችን በማረም በሕዝቡ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚሰራ መግለፃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

