Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ የባሕር በር አስፈላጊነት..

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ የባሕር በር አስፈላጊ ነው አሉ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ኒኮላስ ሲማርድ።

የኢትዮጵያ እና ካናዳ የ60 ዓመታት የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማስመልከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

አምባሳደር ኒኮላስ ሲማርድ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ባሕር በር ፍላጎት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ሰላማዊ ውይይትና ስምምነት እንዲሳካ ካናዳ ታበረታታለች፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ትስስር በማጠናከር ሊፈጠሩ የሚችሉ ውጥረቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለውም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ እያሳየች ያለውን የመሪነት ሚና ካናዳ እንደምታደንቅ ገልጸው÷ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ካናዳ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ከተለመደው የእርዳታ ድጋፍ ወደ የላቀ የኢኮኖሚ ውህደትና የንግድ ትብብር ለማሸጋገር እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

በመድረኩ ካናዳ ባለፈው ዓመት ብቻ 265 ሚሊየን ዶላር በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረጓ የተገለጸ ሲሆን÷ ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚዋ የልማት አጋር አድርጓታል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ምሁራዊ ዕድገት ያበረከተው ታሪካዊ አስተዋፅዖ የተመሰገነ ሲሆን÷ በተለይም በዩኒቨርሲቲው እና በካናዳ የትምህርት ተቋማት መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ትብብር ተጠቃሽ ሆኗል።

እንደ ቶሮንቶ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የአካዳሚክ ጥምረቶች በጤና፣ በትምህርት እና በምርምር ዘርፍ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማፍራት የሀገሪቱን ተቋማዊ አቅም በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሕክምና፣ በምህንድስና፣ በንግድና በስፖርት ዘርፎች እያበረከቱ ያለው አስተዋፅዖ የሁለቱን ሀገራት ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑም ተጠቁሟል።

በዘመን በየነ

Exit mobile version