አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የቋንቋ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
የብዝሃ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ባለቤት የሆነችው ቻይና ቋንቋዋ የዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ እውቅና ያገኘ ሲሆን ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱ ተመላክቷል።
ቋንቋው ቻይና ከኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የቀደመ ግንኙነት ማጠናከሩ ነው የተገለጸው፡፡
የቻይና ቋንቋ በአፍሪካ ያለው ተደራሽነት እየሰፋ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በሀገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ቋንቋ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሰጠት መጀመሩ የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል፡፡
የቻይና ቋንቋ ሀገሪቱ ያላትን ባህልና ሃብት በአግባቡ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ የስልጣኔ መነሻዋ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተገልጿል።
ቀኑ በተባበሩት መንግስታት የቻይና ቋንቋ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ እውቅና ያገኘበት ዕለት ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ የቻይናን ባህል፣ ቋንቋና ኪነጥበብ የሚያሳዩ ዝግጅቶች ቀርበዋል።
በጀማል አሕመድ

