አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ቤን ብላክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ ከ2026ቱ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የጸደይ ስብሰባ ጎን ለጎን የተደረገ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
ሁለቱ ወገኖች በንግድ፣ ኢኮኖሚ፣ ትራንስፖርት እና ማዕድን ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተመላክቷል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የውጭ ኢንቨስትመንት ሁኔታን ለማሻሻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አብራርተው÷ መንግስት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ቤን ብላክ በበኩላቸው÷ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ እየተገነቡ ላሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እና መሰረተ ልማቶች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ትብብርን ለማጠናከር እና በኢትዮጵያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኢንቨሰትመንት ዘርፎች ለማሳደግ ከስምምነት ላይ መደረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

