አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ የመንገድ ኮሪደር ግንባታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ሊፋጠን ይገባል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ።
ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የፀደይ ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደው 28ኛው የአፍሪካ ቀንድ ትብብር የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፋለች።
በመድረኩ በ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ለመገንባት እቅድ በተያዘላቸው ከ9 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የአራት ኮሪደሮች አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ለቀጣናዊ የመንገድ ኮሪደሮች ግንባታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ሊፋጠን ይገባል።
ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ላላት እና የንግድ እንቅስቃሴዋ ሙሉ በሙሉ በቀጣናዊ ትስስር ላይ ለተመሰረተች ሀገር ቀልጣፋ የትራንስፖርት ኮሪደሮች ምርጫ ሳይሆኑ የግድ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።
በኢኮኖሚ ኮሪደሮች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን ማፋጠን የንግድ ልውውጥን ለማሳለጥ፣ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እና የሥራ እድልን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአራት ኮሪደሮች ግንባታ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ከልማት አጋሮች 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ማሰባሰብ እንደተቻለ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
ሚኒስትሮቹ ቀጣናውን ሙሉ በሙሉ ለማገናኘት ወሳኝ በሆኑ ክፍሎች ላይ አሁንም የፋይናንስ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የፋይናንስ መፍትሄዎችን መተግበር ላይ ትኩረት ያደረገው ስብሰባው ቀሪ የዘርፉ ክፍተቶችን በመሙላትና የቀጣናውን ሙሉ የኢኮኖሚ አቅም በመጠቀም ወሳኝ የኮሪደር ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማስፈጸም የተግባር ጥሪ በማቅረብ ተጠናቋል።

