አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሊባኖስ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ እስራኤል ጥላው የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከነገ ጀምሮ ልታነሳ ነው፡፡
የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው ÷ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳል፡፡
ጦሩ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሀገሪቱ ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ እንዲሁም ት/ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉ ይታወሳል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ÷ከሂዝቦላህ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ስጋት ተጋርጦብን ነበር፤ነገር ግን በጦርነቱ ሁሉንም ስጋቶች አስወግደናል ብለዋል፡፡
ሂዝቦላህ ሰርጎ በመግባት በእስራኤል የሚፈፅመውን የሽብር ጥቃት ተከላክለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ቡድኑ ይጠቀምባቸው የነበሩ ከ150 ሺህ በላይ ሚሳኤሎች መውደማቸውን አመልክተዋል፡፡
የቡድኑን ጥቃት ለመከላከል እስራኤል ከሊባኖስ ጋር በምትዋሰንበት ሰሜናዊ አቅጣጫ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማይደረገበት ነጻ ቀጣና እንዲካለል መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

