Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ያላትን ታላቅ ዝና ዳግም ያረጋገጠ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ያላትን ታላቅ ዝና ዳግም ያረጋገጠ ነው አሉ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዛሬ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድርን (Addis Ababa Grand Prix) በድምቀት አስተናግዳለች ብለዋል።

ይህ ስኬት በከተማችን የገነባናቸው ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ውጤት ከመሆኑም ባለፈ ሀገራችን በአትሌቲክስ ዘርፍ ያላትን ታላቅ ዝና ዳግም ያረጋገጠ ነው ሲሉም አመላክተዋል።

በሚያዚያ ወር ብቻ የምናስተናግዳቸው ሦስት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች፣ ከተማችን ማንኛውንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ውድድር የማስተናገድ ብቃትና ደረጃ ላይ መድረሷን የሚያሳዩ ናቸው ነው ያሉት።

ውድድሮቹ ተተኪ አትሌቶችን ከማነቃቃታቸው በላይ ለስፖርታዊ ቱሪዝም ዕድገት የጎላ ፋይዳ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ይህ ታሪካዊ ውድድር በአዲስ አበባ መካሄዱ ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹና ሳቢ ከማድረግ ባለፈ ለዓለም አቀፍ ኩነቶች ማራኪ የስበት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን በተግባር ያሳየ እውነት ነው ብለዋል።

ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተለመደውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት ላሳዩት ስፖርት ወዳድ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

ለእንግዶቻችን በቆንጆዋ አዲስ አበባ የማይረሳና ያማረ ቆይታ እንዲኖራችሁ እመኛለሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፤

Exit mobile version