አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የህብረት ሥራ ማህበራትን አሰራር በማዘመን የማስፈጸም አቅማቸውን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው አለ።
2ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በኮሚሽኑ የህብረት ሥራ ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጣሃ ዲጋ በዚህ ወቅት ፥ 22 ሺህ የህብረት ሥራ ማህበራት በግብርና ዘርፍ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ብለዋል።
ማህበራቱ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት የገበያ ሁኔታ ማረጋጋት፣ በተሻለ ዋጋ የማቅረብና የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ማድረግ ላይ ስኬታማ ሥራ ማከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአርሶ አደሩን የውጭ ገበያ ተሳትፎ በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የላቀ ሚና መጫወታቸውን ነው የገለጹት፡፡
በቀበሌ ደረጃ 9 ሺህ የሚጠጉ የህብረት ሥራ የልማት ሰራተኞች እንደሚገኙ ጠቁመው ÷የማህበራቱን አሰራር በማዘመን የማስፈጸም አቅማቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጅማ ዞን የህብረት ሥራ ማህበራት ጽ/ቤት ኃላፊ ድማሙ ንጋቱ በበኩላቸው ፥ የማህበራቱን የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ ላይ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በወርቅአፈራው ያለው

