አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የህንድ የአፈር ማዳበሪያ ምርት መጠን በ24 ነጥብ 6 በመቶ መቀነሱ ተሰምቷል፡፡
ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን መዝጋቷን ተከትሎ ህንድ የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የምትጠቀምበት የተፈጥሮ ጋዝ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ አለመሆኑ በአፈር ማዳበሪያ ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረሱ ነው የተገለፀው፡፡
የህንድ ንግድ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በፈረንጆቹ 2025 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮ የማዳበሪያ ምርት በ24 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ንግድ በሕዳር ወር ከነበረው የ4 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አሁን ላይ ወደ 3 ነጥብ 4 የቀነሰ መሆኑንም ገልጿል።
የሀገሪቱ ነዳጅ ባለስልጣን የምርት መቀነስ ቢያጋጥምም በቂ የአፈር ማዳበሪያ ክምችት በመኖሩ በቀጣይ ምርቶችን ለሌሎች ሀገራት የመሸጥ እና የማሰራጨት ስራ እንደሚከናወን ጠቁሟል፡፡
ዓለም አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ምርት የሆርሙዝ ሰርጥን ጨምሮ በሌሎች የባህር ትራንስፖርቶች የሚደረግ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል የዓለም ምግብ ምርትን ተፅዕኖ ውስጥ መክተቱ ተገልጿል፡፡
በዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላት ህንድ 45 በመቶ የሚሆነው የሰው ኃይሏ በግብርና ምርት ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ዘ ፔኒንሱላ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ

