Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህብረት ሥራ ማህበራትን በቴክኖሎጂ የማጠናከር ስራ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የህብረት ሥራ ማህበራትን በቴክኖሎጂ የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ነው አለ፡፡

2ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

የሶማሊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን በወቅቱ እንዳሉት፤ ማህበራቱ በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

በክልሉ መታረስ የሚችል 10 ሚሊየን ሔክታር መሬት እንዳለ ገልጸው፤ በእንስሳት ሀብት፣ በሌማት ትሩፋትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምርታማ ለመሆን የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁሉም መስኮች የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የሀገር ኢኮኖሚን መገንባት የሚቻለው በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍና በዜጎች ድምር አቅም መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት የህብረት ሥራ ማህበራትን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቷል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራት ተጨባጭ ሃብት በማፍራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም ፈጥረዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ ናቸው፡፡

Exit mobile version