አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን መገናኛ ብዙኃን የሀገር ግንባታ ሂደትን ለማጠናከርና የወል ትርክትን ለመገንባት በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።
ባለስልጣኑ ከሚዲያ ተቋማት ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር “መገናኛ ብዙኃን ለሀገር ግንባታ እና ለማህበረሰብ አመለካከት ቀረጻ” በሚል መሪ ሐሳብ ውይይት እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መገናኛ ብዙኃን በሚሰሯቸው ስራዎች መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸው÷ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸውም ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም ከመንግስት በኩል ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት አምባሳደር ሬድዋን÷ በመገናኛ ብዙኃን የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረቅና ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል ባለስልጣኑ የውይይት መድረክ ማመቻቸቱን አመላክተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው÷ መገናኛ ብዙኃን ወቅታዊ እና ተዓማኒ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ለማህበረሰብ ቀረጻና ሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል።
በዚህ ረገድም የሕዝብ፣ የግል፣ የክልልና የማህበረሰብ ሚዲያዎች የወል ትርክትን በመገንባት ረገድ ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለመገናኛ ብዙኃን ይዘት መሻሻል በተሰጠው ትኩረት በአይነት፣ በቁጥር እና በጥራት በርከት ያሉ ሚዲያዎችን የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏልም ነው ያሉት።
በውይይት መድረኩ የማህበረሰብ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና የክልል ሚዲያ ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን÷ ያለፉት ሦስት ወራት የመገናኛ ብዙኃን ይዘት ክትትል የአዝማሚያ ትንተና ሪፖርት ቀርቧል።
በእዮናዳብ አንዱዓለም

