Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ የባሕል ለውጥ ያስፈልገዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ሀገር የአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ የባሕል ለውጥ ያስፈልገዋል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎትን በይፋ በመረቁበት ወቅት እንዳሉት፤ የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ ብሎም እያንዳንዱ ዜጋ የባሕል ለውጥ ማድረግ ያስፈልገዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታት በተለይም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለማምጣት ሲሞክሩ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘርፉን በሚፈለገው ልክ በማሻሻል ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ሳይቻል መቆየቱን ገልጸዋል።

ለረዥም ጊዜ የቆየውን ተቋማዊ እና ግለሰባዊ ባሕል ቀይሮ ተገልጋይን አክብሮ በመቀበል አገልግሎት መስጠት ፈታኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎትን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ በለውጡ ከተወሰኑ አምስቱ የልማት ዋና ዋና መሠረቶች አንዱ የሆነውን ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ነው ያብራሩት።

በአንድ ማዕከል ውስጥ ብዙ አገልግሎቶች ለመስጠት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ 45 መድረሱን ጠቅሰው፤ እስከ መጪው መስከረም ድረስ ከ100 በላይ ማዕከሎች ለአገልግሎት እንደሚበቁ ጠቁመዋል።

3 ሺህ የሚደርሱ አገልግሎቶችን በሚሰጡት ማዕከላቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የማዕከላቱ ቁጥር እንደ ኢትዮጵያ ላለ ትልቅ ሀገር በቂ ባለመሆኑ መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት መጀመሩ ሰዎች በአቅራቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

ለዚህ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ኤሌክትሪክ ወይም በሀገር ውስጥ የሚመረትን ጋዝ የሚጠቀሙ ብዙ ተሽከርካሪዎች እየተዘጋጁ በመሆኑ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በስፋት የሚሰራበት እንደሚሆንም አመልክተዋል።

በቂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሠረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ ሥርዓት ያለው በመሆኑ ለተገልጋዮች በአቅራቢያ አገልግሎት በመስጠት ሕይወትን ቀለል ያደርጋል ነው ያሉት።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋይን እርካታ መጨመሩን አንስተው፤ ይህንን በመለማመድ እስከ እጅ ስልክ ድረስ የቀረበ አገልግሎት ወደ መስጠት መገባት አለበት ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version