Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሙስናን ለመከላከል ዲጂታል አገልግሎት ትልቅ ሚና ይጫወታል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሙስናን ለመከላከል ዲጂታል የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎትን ስራ አስጀምረዋል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በወቅቱ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም በአገልግሎት ዙሪያ የተደረጉ የተለያዩ ሙከራዎች ሕብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ አገልግሎት የማግኘት መብቱን ባለማስከበር ብዙ ሰውን ያስመረረ እንደሆነ አስረድተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት የሀገሪቱን እንቅስቃሴ የሚጎትት መሆኑን በማንሳት÷ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ተስፋ የተጣለበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህም በአገልጋይና ተገልጋይ መካከል ያለውን ንክኪ በማጥፋት እንዲሁም በመሀል የሚገቡ የደላሎችን ሰንሰለት በመበጠስ ሕብረተሰቡ አገልግለቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ሥራዎችን በማፋጠንና ተገልጋዩ በፈለገው ጊዜ አገልግሎቱን እንዲያገኝ በማስቻል የሙስና መንገድን በመዝጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

የመንግሥት አገልግሎትን ለማስተካከል የተደረገ ትልቁ ሪፎርም እንደሆነ አንስተው፤ ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በቀላሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል ጥሩ ርምጃ እንደሆነ አውስተዋል።

ሕብረተሰቡ አገልግሎት የማግኘት መብቱን መጠቀምና ግዴታውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

አቋራጭ የሚባሉ መንገዶችን በመተው የዲጂታል አገልግሎቱን ሕብረተሰቡ በትክክል እንዲጠቀም አመልክተው፤ መንግሥት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ስራ እንዲያጠናክር አጽንዖት ሰጥተዋል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version