አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩናይትድ ኪንግደም የባህር ንግድ ኦፕሬሽን ማዕከል በሆርሙዝ ሰርጥ ሶስት መርከቦች በደረሰባቸው ጥቃት አንደኛዋ በእሳት ስትያያዝ ሁለቱ ደግሞ በኢራን ወታደራዊ ኃይል ተይዘዋል አለ።
የአሜሪካ የኢራን የወደብ እንቅስቃሴ እገዳ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የኢራን ወታደራዊ ኃይል በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡
ከኢራን በስተ ምዕራብ በተፈጸመው ጥቃት መርከቦቹ በእሳት ስለመያያዛቸው ከመነገሩ ባለፈ በሰውና በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተባለ ነገር የለም።
ጥቃቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሁለቱ ሀገራት ድርድር መሻሻል እስኪያሳይ ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚያራዝሙ ከተናገሩ በኋላ ነው ተብሏል።
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተያየትን ተከትሎ እስካሁን በኢራን በኩል በይፋ የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ ተገልጿል።
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ አማካሪ እንደተናገሩት የተኩስ አቁም ማራዘሚያው የአሜሪካ ለዳግም ድንገተኛ ጥቃት ጊዜ የመግዛት ዘዴ ነው በማለት አጣጥለዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካካል እየተደረገ ያለው ድርድር ግልጽ የጎደለው ሲሆን፤ በትናንትናው እለት ወደ ፓኪስታን ለድርድሩ እንደሚያቀኑ ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ እስካሁን ፓኪስታን አልገቡም፡፡
በኢስላማባድ የሚገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንዳለው ፓኪስታን ለዳግም ድርድሩ ሁኔታዎችን አመቻችታ እየጠበቀች ቢሆንም የሀገራቱ ተደራዳሪዎች ተገናኝተው የመነጋገራቸው ጉዳይ በዚህ ሳምንት ተስፋ እንደሌለው ጠቅሷል፡፡
በአቤል ነዋይ

