Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አብራሪው ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር የተጋጩት የደቡብ ኮሪያ ተዋጊ ጄቶች …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ነገሩ የተከሰተው በፈረንጆቹ 2021 ላይ ነው።
ሁለት የደቡብ ኮሪያ ተዋጊ ጄቶች በዴጉ ከተማ አየር ላይ ይጋጫሉ፤ የግጭቱ መንስኤ ሲጣራ ቆይቶ አሁን ላይ ውጤቱ ይፋ መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የጦር ጄቶቹ ሊጋጩ የቻሉት የአንደኛው ጄት አብራሪ ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር መሆኑ በምርመራ ተረጋግጧል።
በዚህም በበረራ ላይ ከነበሩት አንደኛው አብራሪ አውሮፕላኑ ወደ ላይ እና ወደ ታች ሲንቀሳቀስ ያለውን ትዕይንት በፎቶ ለማስቀረት ሲሞክር ጄቶቹ መላተማቸው ነው የተነገረው፡፡
በወቅቱ በደረሰው የግጭት አደጋ አብራሪዎቹ ጉዳት ሳይደርስባቸው ማረፍ ችለዋል።
ነገር ግን የጄቶቹ ግጭት በንብረት ላይ የ880 ሚሊየን የደቡብ ኮሪያ ዎን (596 ሺህ ዶላር) ኪሳራ አስከትሏል።
አደጋው የደረሰው በአብራሪው ግዴለሽነት መሆኑ በምርመራ የተረጋገጠ በመሆኑ ከአደጋው በኋላ ከስራ የተሰናበተው አብራሪ 88 ሚሊየን ዎን እንዲከፍል ተወስኗል።
ሆኖም አብራሪው የካበተ ልምድ ያለው በመሆኑ የከፋ አደጋ እንዳይከሰት ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡
ለቅጣቱ ምክንያት የሆነው አብራሪው በጡረታ የሚሰናበት በመሆኑ የመጨረሻ በረራውን ስለያሚደርግ ማስታወሻ ለማስቀረት ፎቶ እንደሚነሳ ተናግሮ እንደነበር ተጠቅሷል።
በባልደረባው እና የሌላኛው ተዋጊ ጄት አብራሪ ላይ የተወሰደ ርምጃ ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version