አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ገበያ በማረጋጋት ተግባር ውጤታማ ሆነዋል አለ የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያና ማደራጃ ኤጀንሲ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱ ሀሰን ያዮ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ በክልሉ የተሰማሩ 1 ሺህ 181 መሠረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ።
የህብረት ስራ ማህበራቱ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ገበያ የማረጋጋት ሚና እየተወጡ እንደሆነ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ ያቀረቡት ማህበራቱ፤ በተለይም አነስተኛ የቁም እንስሳት፣ ዓሣ፣ ወተት፣ ቴምር፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጨው እንዲሁም ሌሎች የፍጆታ ምርቶችን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የምርቶቹ መቅረብ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከግብይቱ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።
ከ2 ዓመት በፊት ወደ ስራ የገባው የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ውጤት እያመጣ በመሆኑ የዚህ ዓመት አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የ9 ወራት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ158 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስረድተዋል።
በከድር መሀመድ

