Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ማረሚያ ቤቶች የነበራቸውን አሉታዊ እይታ የቀየሩ ስራዎች ተሰርተዋል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማረሚያ ቤቶች በህብረተሰቡ ዘንድ የነበራቸውን አሉታዊ እይታ እና ስያሜ መቀየር የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፡፡

የፌዴራልና የክልል ተቋማት አመራሮች በተገኙበት 20ኛው የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ “የማረሚያ ተቋማት ለሀገር ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት÷ የጋራ ጉባኤው ሀገራዊ የሪፎርም እና የተቋማት ግንባታ ስራዎች ውጤታማ በሆኑበት ወቅት መደረጉ ለተጨማሪ ድልና ትጋት ያነሳሳል።

ማረሚያ ቤቶች ከዚህ ቀደም በህብረተሰቡ ዘንድ ይታዩ የነበረው በአሉታዊ መልኩ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፉት ዓመታት የተቋማቱን ገጽታ መቀየር ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የነበራቸው አሉታዊ ገጽታ እና ስያሜ የቀየረ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ የተቋማቱን ገጽታ የመቀየር እና ለህብረተሰቡ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የማረሚያ ተቋማት የሰብዕናና የክህሎት ግንባታ ተቋም ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ እና የታራሚዎች አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉንም ተናግረዋል።

በስመኝ ስዩም

Exit mobile version