አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ዜጎችን ማዕከል ያደረጉና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያካተቱ ናቸው አሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናት እና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ መድረኩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፥ ከተሞች ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት እንዲለሙና ሀብት እንዲያመነጩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ከምናረጋግጥባቸው ጉዳዮች ውስጥ ከተማ ውስጥ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የከተማ ልማትና የመሰረተ ልማት የፖሊሲ ለውጦች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በፊት ከተሞች የመልካም አስተዳደደር እጦት ማሳያና የድህነት ማዕከል እንደነበሩ አስታውሰው፥ አሁን ላይ የብልጽግና፣ የፈጠራና የፍጥነት ማዕከላት ሆነዋል ብለዋል፡፡
ከተሞች የኢኮኖሚና የዕድገት ማዕከል እየሆኑ በመመጣታቸው የዜጎች የአኗኗር ዘዬ መቀየሩን የገለጹ ሲሆን፥ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያካተተ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ የተጀመሩ ስራዎችን በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች በማስፋት 76 የሚሆኑ ከተሞች ላይ መሰል የልማት ስራዎች እየተተገበሩ ነው ብለዋል፡፡
ከተሞች ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲችሉ በተሰሩ ስራዎች የሚያመነጩት ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰው፥ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለዜጎች ኑሮ የተሻለ ከባቢ እየፈጠረ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
መጪው ትውልድ ከአሁኑ የበለጠ ሥራ እንዲሰራ ኃላፊነት የሰጠንበትን ስራ ሰርተናል ያሉት ሚኒስትሯ፥ እያንዳንዱ የመሰረተ ልማት ሥራዎቻችን ዜጎችን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

