Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከአካባቢ ጥበቃ ሚና የተሻገረው አረንጓዴ ዐሻራ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ በአንድ ዓላማ ለልማት ተነስተው ለዛሬ ስንቅ ለትውልድ መሰረት እንዲጥሉ ያስቻለው “አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር” ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር በርካታ ዓላማ አንግቧል።

ችግኝ የመትከል እንቅስቃሴ ቀደም ባሉት ዘመናት ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደተፈጸመው በተደራጀ እና በተቀናጀ መንገድ አልተመራም።

ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መርሐ ግብሩን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ በበልግ፣ በክረምት እና በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ንቅናቄዎች ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኝ በመትከል ዓለምን ያስደመመ ስኬታማ ስራ ተሰርቷል።

መርሃ ግብሩ ከጀመረበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠን እንደ አየሩ ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም አማካይ የጽድቀት ምጣኔ 82 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ኢትዮጵያ በመርሐ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እና የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት ትልቅ ቁርጠኝነት እያሳየች ትገኛለች።

መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ በማድረግ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።

አረንጓዴ ዐሻራ ለደን ሽፋን ማደግ፣ ለደን መጨፍጨፍ መቀነስ እና ለአርሶ አደሮች ገቢ መጨመር አስተዋጽኦ ማድረግ ከጀመረ ውሎ አድሯል።

መርሐ ግብሩ ከተጀመረ እስከ 2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ1 ሚሊየን በላይ የስራ እድል ተፈጥሯል፤ ከ63 በመቶ በላይ ሴቶች በአረንጓዴ ዐሻራ እና አግሮ ፎረስተሪ ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በነባር ዕሴቶች ጠብቆ ያቆያቸውና በጊዜ ሂደት እየተመናመኑ የመጡ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መልሰው እንዲጠነክሩ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ማምጣት በመጀመራቸው ብዝኃ ሕይወቱ መልሶ እንዲያገግምና አካባቢዎቹ የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ መልካም ዕድል ፈጥሯል፡፡

ሀገራዊ የአረንጓዴ ልማት ግንባታ ከዘላቂ ጥቅሞች ተጨማሪ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድሎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው መርሐ ግብሩ ለሌሎች ሥራዎች ግብዓት በመሆን እና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ለማሳካት መሰረት በመጣል አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

መርሐ ግብሩ ለዓለም ምሳሌ ይሆናሉ ተብለው ከተመረጡ ዋና ዋና ሥራዎች መካከልም አንዱ ሆኗል፡፡

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም በሚል ዘርፍ እውቅና መስጠቱ አይዘነጋም።

በዚህም ኢትዮጵያ በመርሐ ግብሩ አማካኝነት የአየር ንብረት ለውጥን ችግር በመረዳት መፍትሄ ለማምጣት ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ችላለች።

ኢትዮጵያን በዚህ ዘርፍ እንድትመረጥ ያስቻላት መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተመራበት አግባብ፣ ለዓለም ስነ ምህዳር ያበረከተችው ትሩፋትና ህዝቡ ያሳየው የነቃ ተሳትፎ ታይቶ መሆኑ ግልጽ ነው።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት ለመርሐ ግብሩ ያለው ቁርጠኝነት ለስኬቱ ዋና መሰረት መሆኑ ይታወቃል።

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version