Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባቡር ትራንስፖርት ድርሻን ወደ 17 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የባቡር ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት በዘርፉ ያለውን ድርሻ ወደ 17 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል አሉ።

ሚኒስትሩ የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናትና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማን ተከትሎ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ ጭነት ለማጓጓዝ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው በዚሁ መሠረት መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ከ15 በመቶ በልጦ የማያውቀውን የባቡር ድርሻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 17 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን፥ ይህም የተሽከርካሪ ድርሻን የቀነሰ ነው ብለዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ከመገንባት አንጻር ወደ ሀገር የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ከማሳደግ በተጨማሪ ከባድ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኤሌክትሪክ የሚጠቀሙ ከባድ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደጀመሩ ገልጸው፥ የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ግዢ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።

ባለፉት 9 ወራት አሰራርን ለማዘመን በተሰራ ስራ ዘጠኝ ሲስተሞችን በማልማት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው፥ የጭነት እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ሥርዓት መተግበሩን አንስተዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version