አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዜጎችን የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው አለ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር።
ሚኒስቴሩ በአዲሱ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት አዋጅ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ይገኛል።
በመድረኩ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪትን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝና በተለይም በህገወጥ መንገድ ዜጎችን ወደ ውጭ በመላክ ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉ አሰራሮችን ለማስቀረት ተገቢው ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በሚኒስቴሩ የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ዳንኤል ተሬሣ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በዘርፉ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያመጡ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገር የስራ ሥምሪት ጉዳዮች በሰጠችው ትኩረት የነበሩ ክፍተቶችን መቀነሥም ሥለመቻሉ ነው ያነሡት።
በተለይም አሰራሮችን ዲጂታል በማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የዜጎች የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ጉዞ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራት ተከውነዋል ነው ያሉት።
ለአብነትም በ2014 ዓ.ም በህጋዊ መንገድ የነበረው የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ከ40 ሺህ ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ላይ ባለፉት 9 ወራት ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ለስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም አዲሱ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት አዋጅ እና ከሀገራት ጋር የተደረሰው የሁለትዮሽ ስምምነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን አስረድተዋል።
በሰለሞን ይታየው

