Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የቴክኖሎጂ አካታችነትን ማረጋገጥ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄልፑት በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የቴክኖሎጂ አካታችነትን ማረጋገጥ ይገባል አሉ።

ኩባንያው በቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትና አካታችነት ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው መድረክ እየተካሄደ ነው።

ዊም ቫንሄልፑት በወቅቱ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉ በፍጥነት እያደገ ይገኛል።

በተለይም የዲጂታል መሰረተ ልማት መስፋፋት ለትምህርት፣ ጤና እና የፋይናንስ ዘርፉን በማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

የዲጂታል መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት ባሻገር ተደራሽነት እና አካታችነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመው፥ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ምርትና አገልግሎቶችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።

ጥራት ያለው ትምህርትና የስራ ዕድልን ለአካል ጉዳተኞች በማቅረብ ረገድ ያለው ክፍተት ማህበራዊ ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን ፈጠራንና ምርታማነትን የሚገድብ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ማስፋትና አካታችነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፥ ለዚህም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ሂደት አካል ጉዳተኞች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ነው ያሉት።

ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማስፋትና ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን ተግባራዊ በማድረግ አካታች የዲጂታል ስርዓትን የመገንባት አቅም እንዳላት አንስተዋል።

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version