አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት ግንባታ በመርካቶ ቅጠል ተራ አካባቢ በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ለመኖር እጅግ ምቹ ያልሆነው የቅጠል ተራ ሰፈርን ወደ ውብ መኖሪያ አካባቢነት ለመቀየር ባለ 8 ወለል የሆኑ 9 ህንጻዎች ግንባታ ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።
በ10 ሺህ ካሬ ላይ የሚያርፈው የህንጻዎቹ ፕሮጀክት ከ500 በላይ ቤቶች እንደሚይዝ ገልጸው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን ንፁህ፣ ለሰው ክብር የሚመጥን ዘመናዊ አኗኗር ያለው መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
እንዲሁም ልጆች ቦርቀው እንዲያድጉ የስፖርት ሜዳ፣ የንግድ ሱቆች እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውለት በጥራት እና በፍጥነት ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።
አካባቢው መንገድ ያልነበረው፣ የተጠላለፉ ገመዶች የበዙበት፣ ነዎሪዎች በድህነት ምክንያት ኑሯቸውን ለመደጎም ቤታቸው ውስጥ ቆጥ ሰርተው አልጋ የሚያከራዩበትና ሰዎች ላይ ቆልፈው በሚሄዱበት ጊዜ በሚፈጠር የእሳት አደጋ የሰዎች ህይወት የሚጠፋበትና ንብረት የሚወድምበት እንደነበረ አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቱ ይህን አስከፊ የዜጎች ህይወትን እንሚቀይር ጠቅሰው፤ መርካቶ አካባቢ ብዙ “ተራ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ፣ ቦንብ ተራ … ጠጋ ብለን ስናያቸው የነዋሪዎቻችን የአኗኗር ሁኔታ እና ገፅታውን የሚያሳዩ ናቸው ነው ያሉት።
ዓላማችን እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ደጋግመን በማውራት ነዋሪው ሆድ እንዲብሰው ማድረግ አይደለም ያሉት ከንቲባዋ፤ መፍትሄውን ሰርተን ህይወቱ እንዲቀየር እና ለሰው ልጆች የሚመጥን የክብር ኑሮ እንዲኖር እዚያው የመኖሪያ ቤት እና የንግድ ቦታዎች እንዲያገኝ ማድረግ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በከተማችን ሰው ተኮር ጉዳዮችን ዋነኛ የስራዎቻችንን ማዕከል አድርገን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ አመልክተዋል።

