አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ሳይነጋገሩ ፓኪስታንን ለቀው ወጥተዋል።
ሚኒስትሩ በፓኪስታን ቆይታቸው ከፓኪስታን ከጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ እና ከጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም አሲም ሙኒር ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በዋነኝነት ያተኮረው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በፓኪስታን አደራዳሪነት በሚደረገው ተዘዋዋሪ ድርድር ላይ ነው።
በዚህም ኢራን ለድርድር ያሏትን አቋሞች ለፓኪስታን ባለሥልጣናት ያሳወቀች ሲሆን፤ ውጤት እስኪገኝ ድረስ በፓኪስታን በኩል የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል መሆኑ ተመላክቷል።
ሚኒስትሩ ከሁለት ቀናት የፓኪስታን ቆይታቸው በኋላም ወደ ኦማን ማቅናታቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች እየወጡ ሲሆን፤ የኦማን ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ ተነግሯል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸውን የድርድር ቡድን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ስቲቭ ዊትኮፍን እና ጃሬድ ኩሽነርን የፓኪስታን ጉዞ እንደሰረዙ ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በጄኔቫ የተደረገው ድርድር ሳይሳካ ቀርቶ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከሁለት ወራት በኋላ ነው።
በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ላይ ቢሆንም የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ ምክንያት የዓለም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል።
በሶስና አለማየሁ

