Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ 74 በመቶ የነበረውን የጭቃ ቤት በ44 በመቶ መቀነስ ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 74 በመቶ የነበረውን የጭቃ ቤት በ44 በመቶ መቀነስ ተችሏል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የከተማ አስተዳደሩ የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በግምገማው ከ5 ዓመት አንጻር የተደረሰበትን በማነጻጸር፣ የተገኙ ውጤቶች እና ተስፋ ሰጪ አፈጻጸሞች እንዲሁም በቀጣይ መስተካከል ያለባቸው ተግባራት መለየታቸውን ጠቅሰዋል።

ከንቲባ አዳነች በጽሑፋቸው በከተማ አስተዳደሩ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀምን ጨምሮ ባለፋት 5 ዓመታት ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት ውስጥ ዋና ዋናዎቹን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም ስር የሰደዱ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችና ችግሮችን በመጋፈጥ የጋራ እሴት ግንባታ ላይ በትጋት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

በዚህም አዲስ አበባን ከሰፈር ፖለቲካ በማውጣት የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷ ይበልጥ በማጎልበት ኢትዮጵያዊን ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊያን ሁሉ ዋና ከተማችን ብለው የሚኮሩባት ከተማ አድርገናታል ብለዋል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አዲስ አበባ ለማድረግ ቃል በገባነው መሠረት የከተማዋን ጎስቋላ ገጽታ በመቀየር 74 በመቶ የነበረውን የጭቃ ቤት በ44 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

ለተማሪዎች የት/ቤት ምገባ ፕሮግራም እና ዩኒፎርም የማቅረብ የትውልድ ግንባታ መከናወኑንና የአዲስ አበባ ህጻናት ቦርቀው የሚጫወቱበት ከ5 ሺህ በላይ የልጆች መጫወቻ፤ እንክብካቤ የሚያገኙበት ከ1 ሺህ በላይ ዴይ ኬር በመገንባት ለወላጆች እፎይታን ማስገኘት ተችሏል ነው ያሉት።

በከተማዋ 30 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላትን በመገንባት ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በየለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ከአስከፊ ሕይወት ወጥተው በተጨባጭ የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የተበከሉ ወንዞች ፀድተው፣ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ እና በቆሸሹ የወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የተሻለ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው መሰጠታቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ጨለማ የነበሩ ጐዳናዎች ብርሃን እንዲሁኑ በማድረግ ለወንጀል ለዝርፊያና ለአስገድዶ መድፈር አጋላጭ የነበሩ አካባቢዎች መቀየራቸውን አብራርተዋል።

የመንገድ ሽፋንን 12 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰው÷ በርካታ የመኪና ማቆሚያዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃዎች፣ ሰፋፊ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ማጣሪያ ማዕከላት እንደተገነቡ አመላክተዋል።

የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከ70 በመቶ በላይ፣ የቤት አቅርቦት 480 ሺህ፣ የከተማዋን የመንገድ እና የአረንጓዴ ስፍራ ሽፋን ወደ 24 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

መዲናዋ ከአፍሪካ 10 ንጹህ ከተሞች መካከል አንዷ እንድትሆን ማደረጉን ጠቁመው÷ በሕዝብ ተሳትፎ እና በመንግሥት በጀት ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን ነው ያስረዱት።

እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መወዳደሪያ ማዕከላት በየአካባቢው ተገንብተዋል፤ አዳዲስ ሆስፒታሎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ሲሆን÷ ነባሮቹም ታደሰው ደረጃውን ለጠበቀ አገልግሎት ዝግጁ ተደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መዲናዋን የቱሪዝም ማዕከል በማድረግ በዘጠኙ ወራት ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማስተናገድ እንደተቻለ አንስተው ÷ በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ የገበያ ማዕከላትን እና የእሑድ ገበያዎችን በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች መስፋፋታቸውን ተናግረዋል።

ስር የሰደደ ቀርፋፋ የአገልግሎት አሰጣጥን እና የጉበኝነት ልምምድ ለመለወጥ የመንግሥት አገልግሎቶችን በ6 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና በአንድ ዲጂታል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት መስጠት እንደተቻለና ቀሪ 5 ማዕከላት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አመልክተዋል፡፡

በግምገማው የተገኙ ስኬቶች እና አፈጻጸሞችን የበለጠ በማጠናከር ከተማዋን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version