አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር በቁጥር ከሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎት በላይ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት የምናረጋግጥበት ወሳኝ ምሰሶ ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
አገልግሎቱ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ከምርት ሉዓላዊነት ወደ ቴክኖሎጂ ልዕልና !
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር በቁጥር ከሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎት በላይ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት የምናረጋግጥበት ወሳኝ ምሰሶ ነው ።
መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ‘የሉዓላዊነት ልብ’ አድርጎ በመቅረጽ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን በራሳችን አቅም በመሸፈን ከውጭ ጫና እና ጥገኝነት ነፃ የሆነ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ነፃነት ለመገንባት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተጋ ይገኛል። ይህ መዋቅራዊ ሽግግር ተግዳሮቶችን ወደ ስትራቴጂካዊ ድል በመቀየር፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ልዕልና በተግባር እያረጋገጠ ነው።
የጀመርነው ግዙፍ ሽግግር አሁን ላይ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ምዕራፍ የተሸጋገረ ሲሆን ይህም መንግሥት ዘርፉን ወደ ላቀ የማምረት ሂደት ለማላቅ ያለውን ጠንካራ አቋም በግልጽ ያሳያል። በሐዋሳ፣ በደብረ ብርሃንና በአዲስ አበባ ወደ ሥራ የገቡት የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካዎች በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ሀገራችን ከቀላል የፍጆታ ዕቃዎች ምርት ወደ ላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማምረት መሸጋገሯን በተግባር አረጋግጠዋል ።
ይህንን ግብ በላቀ ደረጃ ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አቅጣጫችን ከመሠረቱ የተቀየረ ሲሆን መንግሥት ከብዛት ወደ ስልታዊ ጥራት የሚያመራ አዲስ ፖሊሲ ነድፎ ወደ ተግባር ገብቷል። በዚህም ትኩረታችን ተራ ሼዶችን ከማብዛት ይልቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸውንና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጡ ስትራቴጂካዊ ኩባንያዎችን መሳብ ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ አዲስ አቅጣጫ ወጣቱን ትውልድ የላቀ የቴክኖሎጂ ባለቤት የሚያደርግና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ ሰንሰለት ውስጥ ተወዳዳሪና የማይተካ የልማት አጋር እያደረጋት ይገኛል።
ከከፍተኛ ቴክኖሎጂ ትኩረታችን ጎን ለጎን፣ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የዘርፉን የገቢ ምርት ጥገኝነት በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ ነው። እንደ ብረት ማዕድን፣ ማርብል እና ሲሊካ ያሉ ሀገራዊ ሀብቶችን ለኢንዱስትሪዎቻችን ቀጥታ ግብዓት እንዲሆኑ በማድረግ፣ “መግዛት ሳይሆን ማምረት ” በሚለው አዲሱ መርሐችን የውጭ ምንዛሬን ከመታደግ ባለፈ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዐቅም በሚገባ አጎልብተናል። ይህም ኢትዮጵያ የራሷን የከተሞችና የመሠረተ ልማት ዕድገት በራሷ የተፈጥሮ ሀብት የመገንባት አስተማማኝ ዐቅም እንድትፈጥርና በአምራች ዘርፉ ራሷን እንድትችል እያደረገ ነው።
በአጠቃላይ መንግሥት ለዘረፉ የሰጠው ልዩ ቱኩረት እና የወሰዳቸው ቁልፍ ርምጃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ከ800 በላይ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ የመለሰ ሲሆን አጠቃላይ የማምረት ዐቅማችንን ወደ 67 በመቶ ከፍ አድርገውታል። የኢንዱስትሪ ዕድገትን ከስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ጋር በማስተሳሰር ለረጅም ጊዜ ብልጽግና የጣልነው መሠረትም ዛሬ ፍሬ ማፍራት የጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያ ዛሬ የቆመችበት ጽኑ መሠረት ነገን በልበ ሙሉነት እንድንቀበል የሚያስችል ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

