አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን ኢኮኖሚ እና እንደ ሀገር የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሥነ ምህዳርን ፈጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረጓ እና ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ለበርካታ የአውሮፓ እና እስያ ሀገራት ኢንቨስተሮች ተመራጭ እየሆነች መጥታለች፡፡
ለዚህም ሰፊ አምራች ኃይል፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ በቂ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የታክስ እፎይታ፣ ከቀረጥ ነፃ እድሎችና መሰል ለኢንቨስትመንት የተመቻቹ የአሰራር ሥርዓቶች መኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት ያላት የመልከዓ ምድር አቀማመጥ፣ የአፍሪካ ነፃ ገበያ ዕድል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአኅጉሪቱ በሰፊው ተደራሽ መሆን እንዲሁም አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ መኖሪያ መሆኗ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ምቹ የገበያ እድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡
እንደ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ÷ በተያዘው በጀት ዓመት በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሃብቶችን በመልመል ረገድ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር በማስገባት እና በውጭ ምንዛሪ ገቢ አመርቂ ውጤቶች ተመዝገበዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 3 ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨሰትመንት መዳረሻ መሆኗ ተመላክቷል።
እንዲሁም ከ2013 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም 18 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ ያላትን ዕምቅ አቅም መጠቀም የሚያስችል ለውጥ እያመጣች ሲሆን÷ በተለይም በሪፎርሙ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን እየሳበች ትገኛለች፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎችም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለውጭ ምንዛሪ ገቢ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘገብ የተነበየ ሲሆን÷ ይህም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻነት የበለጠ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ

