Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቱሪዝም ለሀገር እድገት ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጎለብቱ የገበታ መርሐ ግብሮች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ መርሐ ግብሮች የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያሳድጉ ናቸው አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፡፡

ሚኒስትሯ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከአባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማልማት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ በማድረግ የመዳረሻ ልማትን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በርካታ የቱሪዝም ስፍራዎችና መዳረሻዎች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ የልማት ሥራዎች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የግሉ ሴክተር በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን በማልማት ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር የማልማት ስራ እና ደረጃቸውን የማሳደግ ተግባራት እንደሚከናወኑም አረጋግጠዋል፡፡

የመስህብ ምዝገባ ሂደትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ አበረታች በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁንም 800 የሚሆኑ የቱሪስት መስህቦች መመዝገባቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ካርታ በማዘጋጀት በኩልም በሲዳማ ክልል የተከናወነው የናሙና ሥራ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅሰው ይህንን በመላ ሀገሪቱ የማከናወን ስራ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Exit mobile version