Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና ሄዳያህ ማዕከል በአፍሪካ ቀንድ ጽንፈኝነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ሄዳያህ ማዕከል በአፍሪካ ቀንድ ጽንፈኝነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ጽንፈኝነትን ለመከላከል የምታከናውነውን ስራ አብራርተዋል፡፡

ማህበረሰቡን መሠረት ያደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የሰላም ግንባታው ዋነኛ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሂዳያህ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አህመድ አል ቃሲሚ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ጥናቶችንና ምርምሮችን በማካሄድ እንዲሁም የሥልጠና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ጽንፈኝነትን ለመከላከል የሚያከናውናቸውን ተግባራት አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን በጎ ተጽዕኖ እና የሰላም ተምሳሌትነት አድንቀው ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች በቀጣናው ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በጥናት ለመለየትና ማዕከሉ በዘርፉ ያካበተውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ኢትዮጵያ በራሷ አውድ እንድትጠቀምባቸው የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።

ዋና መቀመጫውን አቡዳቢ ያደረገው ሂዳያህ ማዕከል አሸባሪነትንና ጽንፈኝነትን በሳይንሳዊ መንገድ ለመከላከል በፈረንጆቹ በ2012 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የልህቀት ማዕከል ነው፡፡

Exit mobile version