Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ትምህርት ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር አሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት “የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀውና በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች በሚቀርቡበት የምክክር መድረክ ላይ ነው።

መድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ሲሆን÷ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ዐበይት ስኬቶችን አቅርበዋል።

በዚህም ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ እንደነበር አመልክተዋል።

ዘርፉን በእጅጉ ተጭነውት ከነበሩ ችግሮች መካከል የመሠረተ ልማት ጥራትና የግብዓት እጥረት፣ የተማሪ-መምህር፣ የተማሪ-ክፍል ጥመርታ አለመመጣጠን፣ ለትምህርት ዓይነቶች ብቁ የሆኑ መምህራን አለመኖርን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የስርዓተ ትምህርት አግባብነትና የመጻሕፍት ተደራሽነት ችግሮች፣ ኢ-ፍትሃዊነትና ኢ-እኩልነት፣ የትምህርት ሴክተሩ ትክክለኛነት መዳከም፣ ዝቅተኛ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መኖር ከብዙ ማነቆዎች ጥቂቶች እንደነበሩ መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

በዚህም በጥናት በተደገፈ መልኩ የትምህርት ዘርፉን ፍላጎቶች እና ተግዳሮቶች በመለየት ከተመዘገቡ ዋና ዋና ለውጦች መካከል የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ፣ የመጻሕፍት ህትመት ስርጭትና ተደራሽነት፣ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት በለውጡ ተግባራዊ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

እንዲሁም የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ማሳደግ፣ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሪፎርም፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ትምህርት መስፋፋት፣ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅትና አስተዳደር መሻሻል፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማደግ ዋነኞቹ በለውጡ ተግባራዊ የሆኑና ውጤት ያስገኙ ሆነው ተመዝግበዋልም ነው ያሉት።

Exit mobile version