አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ26 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡፡
ሚኒስትሯ “የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀውና በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች በሚቀርቡበት የምክክር መድረክ ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በዚህም ዘርፉ ከለውጡ በፊት ሲቸገርባቸው የነበሩ መጠነ ሰፊ ክፍተቶችን በመለየት በተወሰዱ ፈጣን የመፍትሔ ርምጃዎች ሰፊ ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የዜጎችን መብት ጥበቃ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።
አደረጃጀቶችን በመደገፍና ለማጠናከር እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፥ አቅመ ደካማ ዜጎችን የመደገፍና የማገዝ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የ26 ሚሊየን 845 ሺህ 686 ሴቶችን እና 4 ሚሊየን 330 ሺህ 948 ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የሴቶችንና ወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎን በማሳደግ ተጨባጭ ስኬት መመዝገቡን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭ ሆነው ድጋፍ የተደረገላቸውና ከጎዳና ላይ የተነሱ ዜጎች፣ የተሀድሶ አገልግሎት ያገኙ አካል ጉዳተኞች፣ በማህበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች የተሰበሰበው ሀብት ከዘርፉ ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

